አክሊለ ብርሃን መኮንን ኃይለ ሥላሴ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ኢንቬስተር ‹‹ግራንድ ግዮን ሆቴል›› በሚል ስያሜ አንድ ባለ አራት ኮከብና አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል በሰባት ቢሊዮን ብር ወጪ ለመገንባት ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ጋር ከትናንት በስቲያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የሆቴሉን ግንባታ የሚያከናውነው ድንቅነሽ ኩባንያቸው 80 በመቶ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ 20 በመቶ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡
የአፄ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ‹‹ልዑል›› የሚባልበት ዘመን ስላለፈ ‹‹ልዑል አክሊለ ብርሃን የሚለውን ስም አልጠቀም›› በማለት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በረሀ ከጋዜጠኞች ጋር ያስተዋወቋቸው የድንቅነሽ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አክሊለ ብርሃን መኮንን፣ ትናንት በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የግዮን ሆቴልን ለመግዛት በጨረታ ከተሳተፉት 12 የውጪ ኩባንያዎች መካከል ድንቅነሽ ኩባንያ በገንዘብም ሆነ በዲዛይን በልጦ ስለተገኘ የጨረታው አሸናፊ ሆኗል፡፡
ግራንድ ግዮን ሆቴል በሚል ስያሜ አሁን ግዮን ሆቴል ባረፈበት ቦታ ላይ የሚገነባው አዲሱ ሆቴል፣ አንድ ባለአራት ኮከብ ሆቴልና አንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል የሚኖሩት ሲሆን፣ የባለአራቱ ኮከብ ሆቴል ግንባታ በአንድ ዓመት ከአራት ወር ጊዜ ውስጥ ሲያልቅ የባለአምስት ኮከቡ ሆቴል ግንባታ ደግሞ በሶስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡
በግዮን ሆቴል ውስጥ መዋኛ ሥፍራ ላይ ባለ አራት ኮከብ ሆቴሉ እንደሚሠራ፣ የዚህ ባለአራት ኮከብ ሆቴል ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጠው ሆቴል ሙሉ በሙሉ ፈርሶ ባለአምስት ኮከቡ ሆቴል ግንባታ እንደሚጀመር አቶ አክሊለ ብርሃን ገልጸዋል፡፡ ድንቅነሽ ኩባንያ ሁለቱን ሆቴሎች ለማሠራት ወደ ሰባት ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ የሚያደርግ ሲሆን፣ ግዮን ሆቴል ያረፈበትን ቦታና ቁሳቁሶች በዓይነት 100 ሚሊዮን ዶላር የገመተው የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የአዲሱ ግራንድ ግዮን ሆቴል የ20 በመቶ ባለድርሻ ሆኗል፡፡
የድንቅነሽ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አክሊለ ብርሃን እንደገለጹት፣ ድርጀታቸው የሚያስገነባው አዲሱ ሆቴል በአፍሪካ ውስጥ በመጠኑም ሆነ በዓይነቱ ከፍተኛ ጥራት ያለው የመጀመሪያ ሆቴል ይሆናል፡፡
የሄሊኮፕተር ማረፊያዎች እንዲኖሩት ተደርጎ የሚገነባው ይኸው ሆቴል፣ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባዎች በሚደረጉበት ጊዜ የሁሉንም አገሮች መሪዎች ማስተናገድ የሚችሉ የፕሬዚዳንት ልዩ ማረፊያዎች እንደሚኖሩትም ተገልጿል፡፡ የሆቴሉ ዋና መግቢያ የሚሆነው በመስቀል አደባባይ ፊት ለፊት ያለው ሥፍራ ነው፡፡
ኢንቨስትሩ አክሊለ ብርሃን መኮንን ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ኢንቬስት ለማድረግ የሚያስችል የገንዘብ አቅም ያላቸው መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ ከውጪ አገር ባንኮች ይዘው የመጡ ሲሆን፣ ማስረጃው በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ታትሞና በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ታይቶ ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ቀርቧል፡፡
‹‹በሚቀጥለው ሳምንት አዲሱ ግራንድ ግዮን ሆቴል ይቋቋማል፡፡ ሆቴሉ ከተቋቋመ በኋላ ቦርድ ተመስርቶ ሥራዎችን ማከናወን እንጀምራለን፤›› ሲሉ የኢንቬስተሩ ተወካይ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ተናግረዋል፡፡
የሆቴሉን ግንባታ ሥራ ለመጀመር ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ድንቅነሽ ኩባንያ ሆቴሉን ከሚያስተዳድሩ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ጋር ውድድር ሲያካሂድ መቆየቱን የጠቆሙት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፣ በአሁኑ ወቅት ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል፣ ሆቴሉን ለማስተዳደር ዝግጁነቱን የገለጸ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በዓለም ውስጥ 4800 ሆቴሎችን የሚያስተዳድር መሆኑንና በስፋትም ሆነ በጥራቱ በዓለም አንደኛ ደረጃን የያዘ ኩባንያ መሆኑን ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ አስታውቀዋል፡፡
ለሆቴሉ ግንባታ ሰባት ቢሊዮን ብር ገደማ ለማውጣት የተዘጋጁት የሆቴሉ ሥራ ያዋጣኛል ብለው ነው ወይስ ለአገርዎ ልዩ ፍቅር ስላለዎት? በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አክሊለ ብርሃን ሲመልሱ፣ ‹‹እትብቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀበረና ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደ ማንኛውም ሰው ሀብታምም ሆነ ድሃ ተመልሶ ወደ አገሩ ነው የሚመጣው፡፡ አሁን በምኖርበት አገር ገንዘብ ቢኖረኝም፣ አገሬን ለማሳደግ ፍላጎት አለኝ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች መሆኗን የገለጹት አቶ አክሊለ ብርሃን፣ ለወደፊቱ ኩባንያቸው የሆቴሉን ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት በላሊበላና በአክሱም አካባቢ የሚሠራው ሥራ እንደሚኖር፣ ኢንቨስትመንቱም በግዮን ሆቴል ግንባታ ላይ ብቻ እንደማይወሰን አስታውቀዋል፡፡
ድንቅነሽ ኩባንያ በአቶ አክሊለ ብርሃንና በቤተሰቦቻቸው የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን፣ (ድንቅነሽ የአቶ አክሊለ ብርሀን ባለቤት ስም ነው) እንግሊዝ ውስጥ ስምንት፣ ጀርመን ውስጥ ደግሞ ሁለት ኩባንያዎች አሉት፡፡ ዋና መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ያደረገው ይኼው ኩባንያ፣ በስቶክ ኤክስቼንጅ ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራ መሆኑንም አቶ አክሊለ ብርሃን አክለው ገልጸዋል፡፡
ከኢንቨስትመንቱ ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ያደረጉት ተሳትፎ ስለመኖሩ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አክሊለ ብርሃን፣ በድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ ጊዜ ድርጅታቸው እርዳታ የለገሰ መሆኑን፣ አድዋ ውስጥ የንግስት ሳባ ትምህርት ቤትን ማሳደሳቸውን፣ በአዲስ አበባ ቅድስተ ሥላሴ ቤተክርስቲያን 2ሺሕ 500 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት ሥራ መጀመራቸውንና በጅማ አካባቢም የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች መሥራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
‹‹እኛ ለሚጎዳው ሕዝብ መድረስ እንጂ የሠራነውን ሥራ ማስተዋወቅ (publicity) አንፈልግም፤›› ያሉት አቶ አክሊለ ብርሃን፣ በቀጣይ ጊዜዎችም ኩባንያቸው አክሱም ውስጥ በ20 ሚሊዮን ዶላር ሙዚየም ለማስገንባት መወሰኑንና ጅማ ውስጥም ሆስፒታል ለማሠራት ማሰቡን ተናግረዋል፡፡
‹‹አዲሱ ሆቴሉ ሲገነባ በአሁኑ ጊዜ ግዮን ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?›› በሚል ለቀረበላቸው የሪፖርተር ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ጨረታውን ያሸነፍንበት አንደኛው ምክንያት የሠራተኞች ጉዳይ ነው፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሥራውን ለቆ እንዲወጣ አልፈልግም፤ ሆቴሉ ሲገነባ ሠራተኞቹ ለአንድ ዓመትና ለሁለት ዓመት ትምህርት ተሰጥቷቸው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡ ለጡረታ የደረሱ ሰዎች ካሉም የጡረታ ክፍያ እየሰጠን እናሰናብታለን፤›› ብለዋል፡፡

EthioGreen

